ሚያዚያ 22/2018 ዓ.ም
ሰክሰስ ፕላስ ቻሪተብል ኦርጋናይዜሽን እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን በስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ተቋማቱን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የሰክሰስ ፕላስ ቻሪተብል ኦርጋናይዜሽን መስራች እና ዳይሬክተር አቶ ፍሬው መንገሻ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው፡፡
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሀብትንና ሙያዊ ብቃትን ለማቀናጀት ያለመ ነው።
የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን የሚወክል ጥላ ድርጅት ሲሆን፣ ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር፣ ማኅበራዊ ተሳታፊነትና አቅም ግንባታ በጥልቀት ይሰራል። ሰክሰስሰክሰስ ፕላስ ቻሪተብል ኦርጋናይዜሽን ደግሞ በተለያዩ የሰብአዊ እርዳታና የልማት ሥራዎች የሚታወቅ ድርጅት ነው። ይህ የመግባቢያ ስምምነት በተናጠል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጥረቶችን በቅንጅት ለመምራት የተደረገ ይፋዊ ቁርጠኝነት ነው።
የመግባቢያ ስምምነቱ ዋና ዓላማዎች
- በየሶስት ወሩ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ወገኖቻችን የዊልቸር ድጋፍ ማድረግ።
- ለአካል ጉዳተኞች የትምህርት፣ የሙያ ሥልጠና እና የሥራ ዕድሎችን ተደራሽነት ማሳደግ! ሲሆኑ የሁለቱም ድርጅቶች ተወካዮች በስምምነቱ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ (ኢአጉማፌ) እንደ ሰክሰስ ፕላስ ካሉ ድርጅቶች ጋር መሥራቱ የሚታዩ የአገልግሎት ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚረዳ ገልጿል።
የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን
ይህ ስምምነት በመሬት ላይ ያለውን ቅንጅት እንደሚያሻሽል፣ የአገልግሎት መደራረብን እንደሚቀንስ እና ለኢኮኖሚያዊ አቅም ግንባታ እንደሚጠቅም የጠቀሱ ሲሆን ሰክሰስ ፕላስ ቻሪተብል ኦርጋናይዜሽንም በበኩሉ አካታች ለሆነ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
ይህ የፊርማ ሥነ-ሥርዓት በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚደረገውን ድጋፍ ይበልጥ የተቀናጀና አካታች ለማድረግ የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ ነው።
ሁለቱም ተቋማት ስምምነቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለአካል ጉዳተኞች ተጨባጭ ውጤት ወደሚያመጡ ተግባራት ለመለወጥ ቃል ገብተዋል።


